Psalms 5

የጧት ጸሎት

ለመዘምራን አለቃ፤ በዋሽንት የሚዘመር፣ የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ቃሌን አድምጥ፤
መቃተቴንም ቸል አትበል።
2ንጉሤና አምላኬ ሆይ፤
ወደ አንተ እጸልያለሁና፣
ድረስልኝ ብዬ ስጮኽ ስማኝ።

3 እግዚአብሔር ሆይ፤ በማለዳ ድምፄን ትሰማለህ፤
በማለዳ ልመናዬን በፊትህ አቀርባለሁ፤
ፈቃድህንም በጥሞና እጠባበቃለሁ፤
4አንተ በክፋት ደስ የምትሰኝ አምላክ አይደለህም፤
ክፉም ከአንተ ጋር አያድርም።
5እብሪተኞች በፊትህ መቆም አይችሉም፤
ክፉ አድራጊዎችንም ሁሉ ጠላህ።
6ሐሰት የሚናገሩትን ታጠፋቸዋለህ፤
ደም የተጠሙትንና አታላዮችን፣
እግዚአብሔር ይጸየፋቸዋል።
7እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት
ወደ ቤትህ እገባለሁ፤
አንተንም በመፍራት፣
ወደ ተቀደሰው መቅደስህ እሰግዳለሁ።

8 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከጠላቶቼ የተነሣ፣
በጽድቅህ ምራኝ፤
መንገድህንም በፊቴ አቅናልኝ።
9በንግግራቸው ውስጥ እውነት የለም፤
ልባቸው የጥፋት ጐሬ ነው፤
ጕረሯቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤
በምላሳቸውም ይሸነግላሉ።
10አምላክ ሆይ፤ የእጃቸውን ስጣቸው!
ተንኰላቸው መውደቂያቸው ይሁን፤
ከኀጢአታቸው ብዛት የተነሣ አስወግዳቸው፣
በአንተ ላይ ዐምፀዋልና።
11አንተን መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ ግን ደስ ይበላቸው፤
ዘላለም በደስታ ይዘምሩ፤
ስምህን የሚወድዱ በአንተ ደስ እንዲላቸው፣
ተከላካይ ሁንላቸው።

12 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ጻድቃንን ትባርካቸዋለህ፤
በሞገስህም እንደ ጋሻ ትከልላቸዋለህ።
Copyright information for AmhNASV